Event Details

በኩዌት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር አባላት ለዜጎች እና ለአገራቸው ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

27 Sep 2019

በኩዌት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በኩዌት አገር የሚኖሩ ዜጎችን መብትና ደኀንነት ለማስጠበቅ ኤምባሲው በሚያደርገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ በመሆን በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን ለማቃለልና ለሀገራቸው ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በኩዌት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ የዳያስፖራ ክፍል ኃላፊ ሐጂ ሙሐመድአሚን ጀማል በኩዌት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ባዘጋጀው 1ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ኮሚኒቲው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ጠቃሚና ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ስኬት መሰረቱ የኮሚኒቲው አመራር ቁርጠኝነትና የዜጎች ተቆርቋሪነት ስሜት መኖሩ ነው ብለዋል። ኃላፊው የታላቁ ህዳሴን ግድብ ቦንድ በመግዛት የኩዌት ነዋሪ ኢትዮጵያውን አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር ጠቁመው፤ በቀጣይም ግድቡን ጨምሮ ለሌሎችም አገራዊ ልማት ዕቅዶች ይኸንኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት የኮሚኒቲ ማህበሩን የ1ዓመት ጉዞ አስመልክቶ በማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሲሳይ ተሾመ አጭር ሪፖርት ቀርቧል። ሊቀመንበሩ ዓላማውን እንደሌሎች አገራት የኮሚኒቲ ማህበራት ለዜጎች ችግሮች ፈጥኖ ደራሽና ለአገራዊ የልማት አጀንዳዎች የተቻለውን ድጋፍ የሚያደርግ ጠንካራ ስብስብ መፍጠር አድርጎ በአዲስ መልክ ከዓመት በፊት የተመሰረተው ኮሚኒቲ ማህበሩ፥ ዜጎች የሚደርስባቸውን ችግር በማቃለል፣ በሆስፒታሎችና በእስር ቤቶች ጉብኝቶችን በማድረግ፣ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሃብት በማሰባሰብ እንዲሁም በባህል ማስተዋወቂያ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ከኤምባሲው ጋር በቅርበት መሰራቱን በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

የኮሚኒቲ ማህበሩ አመራርና አባላት ከኤምባሲው ጋር በመሆን በዜጎች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በመከላከልና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ለአገራዊ የልማት ዕቅዶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የገቡ ሲሆን፤ በዜጎች ድጋፍ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ላደረጉ አባላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።