Event Details

123ኛው የአድዋ ድል በዓል በኩዌት ተከበረ

28 Feb 2019

በኩዌት የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አዘጋጅነት 123ኛውን የአድዋ ድል በዓል በኩዌት የኢፌዲሪ ኤምባሲ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያያን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የካቲት 21/2011 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በዓሉን በማስመልከት ክቡር አምባሳደር ባደረጉት ንግግር አባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀው የጣሊያን ጦር ጋር ተዋግተው ያስገኙት አኩሪ ገድል ለመዘከር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የድል ቀኑን በየአመቱ የካቲት 23 በደማቅ ሁኔታ እንደሚያከብርና የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች የድል በዓል እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም የዘንድሮውን የአድዋ ድል በዓል ልዩ የሚያደርገው ሀገራችን በለውጥ ጎደና እየገሰገሰች፣ በመደመር ቀመር እየተጓዘች እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የነበረውን የረዥም ጊዜ ያለመግባባት ችግር በፈታችበት ማግስት መከበሩ ነው ብለዋል።
ኮሙዩኒቲው የሀገራችንን አኩሪ እሴቶች በማስተዋወቅ፣ የገጽታ ግንባታ ላይ በመሳተፍ፣ የዜጎችን ጥቅምና ደህንነት በማጠበቅ ረገድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ እንደሆነ በመግለጽ፤ ኤምባሲው ለኮሙዩኒቲው መጠናከር ተገቢውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።
በበዓሉ ላይ መነባንብ/ግጥም፤ በተለያየ እምነት ተከታዮች መካከል ተቻችሎ የመኖር ባህል፣ የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በርስ ተግባብቶና ተቻችሎ የመኖርና ከውጭ በመጣ ወራሪ ኃይል ላይ አንድ አይነት አቋም ያለን መሆኑን የሚያንጻብርቅ ተውኔት የቀረበ ሲሆን የብሄር ብሄረሰቦች ሙዚቃዊ ውዝዋዜም ቀርቧል።
በዕለቱ ኮሙዩኒቲ ሟህበሩ ባለፉት 6 ወራት የዜጎች ጥቅምንና ደህንነትን በተመለከተ ያከናወናቸውን ሪፖርትና በቀጣዮቹ 6 ወራት የሚሰራቸውን ስራዎችም በእቅድ አስቀምጧል። በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት የተጓደሉ የኮሙዩኒቲው አመራሮችን ለመተካት ምርጫ አካሄዷል።